ከብሔራዊ ቲያትር ወደ ኮሜርስ የሚወስደው የእግረኛ መንገድ ጥገና ስራ እየተከናወነ ነው

ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከብሔራዊ ቲያትር ወደ ኮሜርስ የሚወስደውን የእግረኛ መንገድ እየጠገነ ነው፡፡ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ ከሚያከናውናቸው ዘርፈ ብዙ የመንገድ ጥገና ስራዎች ውስጥ አንዱ የሆነው የእግረኛ መንገድ ጥገና ስራ ነው፡፡ በተከማዋ በተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ የተጐዱና ለእግረኛ እንቅስቃሴ ምቹ ያልሆኑ የእግረኛ መንገዶችን በመለየት የጥገና ስራ እያከናወነ ይገኛል፡፡ከብሔራዊ ቲያትር ወደ ኮሜርስ የሚወስደው የእግረኛ መንገድ በግራና በቀኝ በኩል አጠቃላይ 1.1 ኪ.ሜ ርዝመት እና ከ 5 እስከ 14 ሜትር የጐን ስፋት ያለው ሲሆን የድሬኔጅ እና የከርቭ ስቶን ስራዎችን ባካተተ መልኩ የጥገና ስራው እየተከናወነ ይገኛል፡፡

ከእሳት አደጋ – አወልያ ት/ቤት የሚወስደው መንገድ የጥገና ስራው ተጠናቆ ለትራፊክ ክፍት ሆኗል

ሚያዝያ 15 ቀን 2013 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከእሳት አደጋ ወደ አወልያ ት/ቤት የሚወስደውን መንገድ የጥገና ስራ አጠናቆ ለትራፊክ ክፍት አድርጓል፡፡140 ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መንገድ ረጅም ጊዜ በማገልገሉ ምክንያት የተጐዳና የተቦረቦረ ነበር፡፡ መንገዱ እንደ አዲስ መጠገኑ በተካባቢው ለሚገኙ ተቋማትና መንገዱን ለሚጠቀሙ የአካባቢው ነዋሪዎች እንቅስቃሴ ምቹ እንዲሆን አድርጓል፡፡በተመሳሳይም ከላንቻ ወደ ቄራ የሚያስወጣው አቋራጭ መንገድ የጥገና ስራ እየተከናወነለት ይገኛል፡፡ ይህ መንገድ በግንባታ ላይ ለሚገኘው ከፑሽኪን አደባባይ – ጐተራ ማሳለጫ መንገድ በተለዋጭነት እያገለገለ ያለ በመሆኑ በመንገዱ መጐዳት ምክንያት የሚኖረውን የትራፊክ መጨናነቅ ለመቀነስ ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡

በቦሌ ክፍለ ከተማ የአርሶ አደሮች መኖሪያ አካባቢ በጠጠር ተደራሽ መንገድ ግንባታ ስራ ተጀመረ

ሚያዝያ 14/2013 ዓ.ም አዲስ አበባ፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን በቦሌ ክ/ከተማ በሁለት አካባቢዎች 5.4 ኪሎ ሜትር ዝርመት የሚሸፍኑ በጠጠር ደረጃ ተደራሽ የመንገድ ግንባታ ስራ ጀምሯል፡፡ ባለስልጣኑ በያዝነው ወር መጀመሪያ ላይ በከተማዋ በተለያዩ አካባቢዎች ለሚኖሩ የአርሶ አደሮች በጠጠር ደረጃ የተደራሽ መንገዶችን የማስገንባት ስራ የአዲስ አበባ ከተማ ም/ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አበቤ እና የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት በንፋስ ስልክ ላፍቶ ክ/ከተማ በይፋ መጀመሩ ይታወሳል፡፡ የዚህ የመንገድ ስራ አካል የሆነው በቦሌ ክ/ከተማ ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የተደራሽ መንገድ ግንባታ ስራ ተጀምሯል፡፡በማስጀመሪያው ላይ የተገኙት የቦሌ ክ/ከተማ ከተማ ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብዲሳ ቱሳ ከዚህ ቀደም በአካባቢው ደረጃውን የጠበቀ መንገድ ባለመኖሩ የመቃረቢያ መንገድ ጥያቄ ከአርሶ አደሩ በተደጋጋሚ የሚጠየቅ ነበር ብለዋል፡፡ በመሆኑም የመንገድ ግንባታው መጀመሩ የህዝቡን ጥያቄ ከመመለሱ በተጨማሪ የአርሶ አደሩን ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚያሳድግ ይሆናል ብለዋል፡፡በአካባቢው የሚገኙ አርሶ አደሮች ተወካይ የሆኑት አቶ አለማየሁ ገረመው እንደተናገሩት በአካባቢው የነበረው መንገድ ለእንቅስቃሴ አመቺ ባለመሆኑ የመውጫና የመግቢያ መንገድ ችግር እንደነበረ ገልፀዋል፡፡ አቶ አለማየሁ አክለውም ያመረትነውን ምርት ወደ ከተማ ለመውሰድ በጣም አዳጋች እንደነበረ አስታውሰው አሁን ለረጅም ጊዜ የነበረብንን ችግር የሚቀርፍ መንገድ መሠራቱ በኑሮአችን ላይ ትልቅ ለውጥ የሚያመጣ ይሆናል ብለዋል፡፡ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የምስራቅ አዲስ አበባ መንገድ ሀብት አስተዳደር ዳይሬክተር ኢንጂ. ልጅአለም ያለው ስለ ግንባታው ሲገልጹ 13 ሚሊየን ብር በጀት ተመድቦላቸው የሚገነቡት ተደራሽ መንገዶች አጠቃላይ ርዝመታቸው 5.4 ኪ.ሜትር ርዝመት ይኖራቸዋል ብለዋል፡፡ በቦሌ ክፍለ ከተማ በሁለት ቦታዎች የሚገነቡት መንገዶች የመጀመሪያው ከሪፌንቲ – ወረገኑ 3.6 ኪ.ሜ ርዝመት ያለው ሲሆን ሌላው ኦሾ በሚባለው አካባቢ የሚሠራው መንገድ 1.8 ኪ.ሜ ርዝመት እንደሚኖረው ገልፀዋል፡፡ኢንጂነር ልጃለም እንዳሉት የመንገድ ግንባታውን በስድስት ወራት ውስጥ ለማጠናቀቅ ውል የተገባ ቢሆንም መጪው ክረምት ከመግባቱ በፊት በተቻለ ፍጥነት ሰፊውን የመንገድ ክፍል ስራ ለማጠናቀቅ ጥረት እንደሚደረግ ተናግርዋል፡፡ እነዚህ የጠጠር አክሰስ መንገድ ግንባታ ስራዎች ተጠናቀው ለአገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ በከተማዋ ዳርቻ አካባቢ የሚኖሩ አርሶ አደሮችን በመንገድ መሠረተ ልማት ተጠቃሚ ያደርጋል፡፡

#አዲስአበባን አዲስአበባን በአዲስ መንገድ!!!

የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ አመራሮች በግንባታ ላይ የሚገኙ የመንገድ ፕሮጀክቶችን ጎበኙ

አዲስ አበባ፣ ግንቦት 16 ቀን 20113 ዓ.ም፡- የአዲስ አበባ ከተማ መንገዶች ባለስልጣን ከፍተኛ አመራሮች በከተማዋ የተለያዩ አካባቢዎች የሚገኙ 10 የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክቶችን ግንቦት 14 ቀን 2013 ዓ.ም ተዘዋውረው ጎብኝተዋል፡፡

ጉብኝቱ የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የ9 ወራት ሪፖርት መሬት ላይ ካለው ነባራዊ ሁኔታ ጋር ለማነፃፀርና በበጀት ዓመቱ የሚጠናቀቁ የመንገድ ፕሮጀክቶች የደረሱበትን የግንባታ አፈፃፀም ለመገምገም ያለመ መሆኑን ጉብኝቱን ሲመሩ የነበሩት የባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የኦፕሬሽን ዘርፍ ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ዘሪሁን ይፍሩ ተናግረዋል፡፡

በዕለቱ ጉብኝት ከተደረገላቸው የመንገድ ፕሮጀክቶች መካከል ከፑሽኪን አደባባይ ጎተራ ማሳለጫ፣ቦሌ ሚካኤል -ካባ መግቢያ -ቡልቡላ 40/60፣ ከቦሌ አለም ዓቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ጎሮ፣ ከወሎ ሰፈር ኡራኤል፣ ከቁስቋም እንጦጦ፣ የእንጦጦ የመኪና ማቆሚያ ግንባታ ፕሮጀክትና ሌሎችም ይገኙበታል፡፡